24ተኛው አዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ ንግድ ትርኢት በመጭው ሐሙስ ይከፈታል

አዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከሚያዘጋጃቸው ዓለም አቀፍ ንግድ ትርኢቶች ውስጥ ለ24ተኛ ጊዜ የሚያዘጋጀው አዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ ንግድ ትርኢት በመጭው ሐሙስ የካቲት 12 ቀን 2012 ዓ.ም አዲስ አበባ በኤግዚቢሽን ማዕከል በደማቅ ሁኔታ ይከፈታል፡፡ በንግድ ትርኢቱ ላይ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችን ጨምሮ፤ የመንግስት ባለስልጣናት፤ ነጋዴዎችና የንግድ ትርኢቱ ተሳታፊዎች ይገኛሉ፡፡ ይህ የንግድ ትርኢት ከአስር \10\ ሀገራት የመጡና ሰማኒያ \80\ የሚሆኑ ዓለም አቀፍ ተሳታፊ ኩባንያዎችን ጨምሮ አንድ መቶ ሃያ \120\ የሀገር ውስጥ ተሳታፊዎች የሚሳተፉበት ሲሆን በዋናነት ከጣሊያን፤ ሱዳንና ዱባይ የመጡ የውጭ ሀገር ተሳታፊዎች ይገኙበታል፡፡

ይህን መሰል ዓለም አቀፍ ንግድ ትርኢት የንግድ ለንግድ ትስስርን ለመፍጠር፤ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ፤ የንግድ ሽርክና ለመመስረትና፤ አዳዲስ ምርቶችን ለማስተዋወቅ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ የውጭ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ እያሳዩት ያለው አበረታች ፍላጎት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ትልቅ ገበያና አበረታች የኢንቨስትመንት ሁኔታ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ያለው አስተዋጽኦ የላቀ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ንግድ ትርኢቶችም ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡ አዲስ አባባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትም ከተቋቋመበት ዓላማ አንጻር ዓለም አቀፍ ንግድ ትርኢቶችን በማዘጋጀት ንግድና ኢንቨስትመንትን በማበረታታትና በማነቃቃት ሚናውን እየተወጣ ይገኛል፡፡

24ተኛው አዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ ንግድ ትርኢት የካቲት 12 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማእከል በደማቅ ሁኔታ ተከፍቶ ለ7 ተከታታያ ቀናት ለጎብኚዎች ከፍት እንደሚሆን ከምክር ቤቱ የተገኝው መረጃ ይጠቁማል፡፡ በዚህ ንግድ ትርኢት ላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ተሳታፊዎች ምርትና አገልግሎታቸውን ይዘው የቀረቡ ሲሆን ጎብኚዎች ከየካቲት 12 ቀን 2012 ዓ.ም እስከ የካቲት 18 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ በኤግዚቢሽን ማዕከል በመገኝት መጎብኝት እንደሚችሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡  

Our Sponsors

User login

 

Contact us

Addis Ababa Chamber of Commerce and Sectoral Associations, Trade and Investment Promotion Department

+ 251115 504647/48 OR +251911 212179

Fax: +251 11 550 4649